ትራምፕ የአሜሪካ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለሩሲያ “አጋርተዋል“ የሚል ወቀሳ እየቀረበባቸው ነው – American President Donald Trump Accused of Revealing Classified Information To Russians

                                         

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አይኤስን የተመለከቱ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለሩሲያ ሁለት ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ባለስልጣናት “አጋርተዋል“ የሚል ትችት እየቀረበባቸው ነው።

ዋሽንግተን ፖስት እና ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጦች ይዘውት በወጡት ትንታኔ ፕሬዚዳንቱ የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት በሚስጥር የያዟቸውን መረጃዎችን ባለፈው ሳምንት በኋይት ሀውስ ተቀብለው ላነጋገሯቸው የሩሲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭና በዋሽንግተን የሞስኮ አምባሳደር ሰርጌ ኪስልያክ ይፋ አድርገዋል ነው ያለው።

ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ሳምንት የኤፍ ቢ አይ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜን ከስልጣን ካሰናበቱ በኋላ በማግስቱ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እና በዋሽግተን የሩሲያ አምባሳደር ሰርጌ ኪስልያክን ተቀብለው ማነጋገራቸው የአሜሪካን መገናኛ ብዙኃን ትኩረትን ስቧል።

ትራምፕ ለሞስኮ የዲፕሎማሲ ሰዎች የሰጡት መረጃ በአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣናት መካከል እንኳ በዝርዝር እርስ በርስ መነጋገር የማይቻልባቸውን ጥብቅ የውጭ ጉዳይ መረጃዎችን ነው ሲሉ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የደህንነት ሰዎችን ከሃላፊነታቸው የሚያነሱት በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከሩሲያ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ይፋ እንዳያደርጉባቸው ለመደበቅ ነው የሚሉ ወቀሳዎች እየተነሱባቸው ባለበት ወቅት ጥብቅ ሚስጥራዊ መረጃዎችን አጋርተዋል መባሉ ሁኔታውን አሳሳቢ እንደሚያደርግም ተመልክቷክል።

ዋሽግተን ፖስት ጋዜጣ ትራምፕ አሁን ለሞስኮ ባለስልጣናት ይፋ ያደረጉት አይኤስ የሽብር ቡድን አዳዲስ የጥቃት ስልቶችን ሊጠቀም ማቀዱን በተመለከተ ሲሆን፥ አያይዘውም ይህን መረጃ ለአሜሪካ ያቀበሉ አጋር ሀገራትን መጥቀሳቸው ነው ያስወቀሳቸው።

ምክንያቱም ሞስኮ የአሜሪካ የደህንነት መረጃ ምንጭ አጋር ሀገራትን ማወቋ የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት በየጊዜው የሚገኟቸውን ጥብቅ መረጃዎች በቀላሉ እንድታውቅ ስለሚያደርጋት ነው ይላሉ በውጭ ጉዳይ ፖሊስ ላይ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው።

ትራምፕ አይኤስ በቀጣይ በአውሮፕላን በረራዎች ላፕቶፕና ሌሎች የኤሌክሮኒክስ ውጤቶችን ተጠቅሞ በተጓዦች ላይ ጥቃት ለማድረስ ማቀዱን ለዋሽንግተን ያቀበሉ ሀገራትን ለሩሲያ ይፋ አድርገዋል፤ ይህ ደግሞ አሜሪካ ከመረጃ ምንጭ አጋር ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ያሻክረዋል እየተባለ ነው።

ትራም አይኤስ ስለነደፋቸው የጥቃት ስልቶች አሜሪካ ያገኘቻቸውን መረጃዎች እንዴት እንደተገኙ እና የመረጃ ምንጮቹ እነማን እንደሆኑ ለሰርጌ ላቭሮቭ ማጋራታቸው ነው ያስኮነናቸው።

በእርግጥ ፕሬዚዳንቱ በጥብቅ የተያዙ ሚስጥራዊ መረጃዎችን እንደ የደረጃቸው እያዩ ይፋ የማድረግ ስልጣን ቢኖራቸውም የመረጃ ምንጭ የሆኑ ሀገራትን ፈቃድ መጠየቅ ግን ግዴታቸው ነው።

አሁኑ ግን በአይኤስ የሽብር እንቅስቃሴ ላይ የተሰበሰቡ መረጃዎች እንዴት እንደተገኙና ከእነማን እንደተገኙ ዋሽንግተንን በባላንጣነት ለምትመለከታት ሞስኮ ማቀበላቸው በአሜሪካ የስለላና የደህንነት ተቋማት ሚስጥራዊነት ላይ ስጋትን ፈጥሯል።

በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት የፕሬዚዳንቱ የብሔራዊ የደህንነትና የፀጥታ አማካሪው ኤች አር ማክማስተር “መረጃው እውነታነት የሌለው ሲሆን ፥ ሩሲያ እና አሜሪካ በሚያገናኟቸው የተለመዱ የፀረ ሽብር እንቅስቃሴዎች ላይ ብቻ ነው የተወያዩት” ይላሉ፡፡

ትራምፕ ይህን ጥብቅ መረጃ ይፋ ማድረጋቸው በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዙሪያ በቂ ልምድ እንደሌላቸው ማሳያም ነው ተብሏል።

የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ተቋም ሲ አይ ኤ እና ብሔራዊ የደህንነት ኤጀንሲ ኤን ኤስ ኤ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ምንጭ፦ቢቢሲ እና ዋሽንግተን ፖስት

Advertisement