የጤና መረጃ ጥራትና አጠቃቀምን የሚያዘምን ፕሮግራም ይፋ ሆነ

                                      
በሃብታሙ ተክለስላሴ

የጤና መረጃ ጥራትና አጠቃቀምን የማዘመን ፋይዳ ያለው ፕሮግራም ይፋ ሆነ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የዘጠኙ ክልሎች ጤና ቢሮዎችና የተመረጡ አምስት ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች ፕሮግራሙን በጋራ ተግባራዊ ለማድረግና በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

በስምምነቱ መሰረት ሚኒስቴሩ የአስተባባሪነት፣ የክልል ጤና ቢሮዎች የፕሮግራሙን ትግበራ የሚቆጣጠሩ ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎቹ በየክልሎች በሚገኙ ወረዳዎች የጤና መረጃ ስርዓትን አስመልክቶ የቴክኒክ ድጋፍና የአቅም ግንባታ ስልጠና ይሰጣሉ።

የአቅም ግንባታና ክትትል(ሜንቶርሺፕ) የሚል ስያሜ ያለው ፕሮግራም ለሶስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፥ ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ የሚውለው 345 ሚሊየን ብር በሚኒስቴሩና በአጋር ድርጅቶች የሚሸፈን ይሆናል።

የአዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ሐረማያ፣ ጅማና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር እንዲሰሩ የተመረጡ ናቸው።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ እንደገለጹት፥ ፕሮግራሙ የመረጃ ስርዓቱን በማዘመን ወጥነት ያለው የጤና መረጃ ስርዓት እንዲኖር ማድረግ ዋነኛ ዓላማው ነው።

የጤና መረጃ አሰባሳቡን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የጤና አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻልም ገልጸዋል።

ከቤት እስከ ማእከል ያለውን የጤና መረጃ ወረዳን መሰረት አድርጎ በመሰብሰብ፥ ለፖሊሲ ቀረፃ መሰረታዊ ግብዓት ሆኖ እንዲያገለግል ያግዛልም ተብሏል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በፕሮግራሙ መሰረት በየክልሉ በሚገኙ ወረዳዎች ላሉ የጤና ባለሙያዎችና አመራሮች የጤና መረጃ አሰባሰብ አቅማቸውን እንደሚገነቡ ተናግረዋል።

ወረዳዎችን የመረጃ ማዕከል በማድረግ የወረዳ ጤና ተቋማት፣ በክልል ጤና ቢሮዎችና በሚኒስቴሩ መካከል የተሳለጠ የጤና መረጃ ፍሰት እንዲኖር የሚያስችል ስራ እንደሚከናወንም አንስተዋል።

የጤና መረጃ አሰባሰብ ዘመናዊ መሆኑ ህብረተሰቡ በጤና ተቋማት የሚፈልጋቸውን መረጃዎች በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያግዝና በየክልሉ በሚገኙ የዞንና ወረዳ የጤና ተቋማት የሚቀርቡ የሀሰት ሪፖርቶችንም ለመቆጣጠር እንደሚያስችል አብራርተዋል።

የክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊዎች በበኩላቸው ፕሮግራሙ በሰነድ መረጃ ይሰበሰብ የነበረውን የጤና መረጃ በማዘመን የመረጃ አጠቃቀምና ጥራትን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

ከወረዳ የጤና ተቋማት እስከ ፌደራል ደረጃ ያለውን የመረጃ ፍሰት የተቀናጀ በማድረግ ህብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን የጤና መረጃዎች ተደራሽ ለማድረግም የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

 

Advertisement