የጤና ችግሮቻችን ለህክምና ባለሙያዎች ለመናገር ማፈርና መሸማቀቅ የለብንም

 

ወደ ጤና ባለሙያ ከምንሔድባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ስለ ግል የጤና ችግሮቻችን ለመናገር ነው፡፡ ይሁን እንጅ አንዳንድ የጤና ችግሮች ከሌሎቹ የበለጠ ሌሎች ሰዎች ሊያውቋቸው አይገባም የምንላቸው አይነት ናቸው፡፡ ለማውራት ያሳፈርዎት በሙሉ የህክምና ባለሙያዎች ከዚህ በፊት ሰምተውት ስለሚያውቁ ለመናገር አይፈሩ!! ከባድ ነገር ቢኖርብንም እንኳን እርዳታ ለመፈለግ በሃፍረት መሸማቀቅ የለብንም፡፡ አርዳታ ለመጠየቅ ከምንሸማቀቅባቸው ጉዳዮች መካከል፡-

1)የአባላዘር በሽታ
ሰዎች የአባላዘር በሽታ እንዳለባቸው ለማወቅ በየጊዜው ወደ ሐኪም ቤት ይሄዳሉ፡፡ የፍቅር ወይም የትዳር ጓደኛችን ለአባላዘር በሽታ መጋለጣችንን ከነገሩንና ምንም አይነት ምልክት ካልታየብን ወደ ሐኪም መሄዱን ትተን ነገሮች ጥሩ ይሆናሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ዳሩ ግን ለመዳንም ሆነ በሽታውን ወደ ሌሎች ላለማስተላለፍ መመርመሩ ጠቃሚ ነው፡፡ እንደ ጨብጥ ያሉ በሽታዎች በግልፅ የሚታዩ ምልክቶች ሲኖሯቸው ሌሎች መሰል በሽታዎች እንዳለብን እንኳ ለማወቅ እንቸገራለን፡፡ የብልት ሀርፐስ ሲጀመር ቢታወቅም አንዳንድ ጊዜ ምንም አይነት የበሽታው ምልክት ከማይታይበት ሰው ሊተላለፍ ይችላል፡፡
2)ከመጠን ያለፈ ላብ
በጋለ ፀሐይ ስር ስንቆም ወይም በህዝብ ፊት ንግግር ስናደርግ ሰውነታችን ላብ ማመንጨቱ የተለመደ ነው፡፡ ሊያልበን በማይገባ ጊዜ ካላበን ግን Hyperhidrosis የተሰኘ የጤና ችግር እንዳለብን ሊያመላክት ይችላል፡፡ በላብ ምክንያት ልብሳችንን ቶሎ ቶሎ ከቀየርን፤ በቀን ከአንዴና ሁለቴ በላይ ሻወር ከወሰድን፤ ስንጨነቅ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስንሰራ እጆቻችን ከረጠቡ፤ አሊያም እቃዎችን መያዝ ካቻልን ወደ ጤና ባለሙያ ዘንድ መሄድ ይኖርብናል፡፡ ከመጠን ያለፈ ላብ ለችግሩ ህክምና ስላለው ችግሩን ለጤና ባለሞያ መግለፅ ጠቃሚ ነው፡፡ ችግሩ ያለብን እኛ ብቻ እንዳልሆንን መገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡ Hyperhidrosis ከሌለብን እንኳ ከመጠን ያለፈ ላብ የሌሎች ጤና ችግሮች የጎንዮሽ ምልክት ሊሆን ስለሚችል መመርመሩ ይመከራል፡፡
3)የብቸኝነት ስሜት
በርካታ የስነልቦና ባለሞያዎች እንደሚሉት ለአብዛኛዎቹ ታካሚዎቻቸው ስለወሲብ ማውራቱ አያስቸግራቸውም ይልቁንም ይበልጥ የሚያሳስባቸው ከሌሎች ሰዎች ጋር ስሜታዊ ትስስር የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ሰዎች የማህበረሰቡ አካል እንደሆኑ አይሰማቸውም፡፡ የሆነ አይነት ችግር እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ ጥቂት ጓደኛ ቢኖራቸውም እንኳ ጥልቀት ያለው ግንኙነት አይመሰርቱም፡፡ ፍላጎቱ እያላቸውም በብቸኝነት ይጠቃሉ፡፡ ችግራቸውን ለመናገርም ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል፡፡ ቀስ በቀስ ግን ያለባቸውን ችግር ማውጣታቸው አይቀርም፡፡
4)ለረጅም ጊዜ የብልት መቆም (priapism)
ለረጅም ጊዜ የብልት መቆም በህመም ስሜት የታጀበ ከመሆኑም ሌላ በጊዜው ካልታከመ ቀዶ ህክምና ሊያስፈልገው ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ስንፈተ ወሲብን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ደግነቱ እንደዚህ አይነት ችግር ሊገጥም የሚችለው በመድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ነው፡፡ ሀኪም መድሃኒት ሲያዝልን ፋርማሲስቱን ስለ አጠቃቀሙ ለመጠየቅ ማፈር የለብንም፡፡ በግልፅ እንዲያብራራልን ካስፈለገ ሰዎች ገለል ሲሉ ጥያቄ ማቅረብ ተመራጭ ነው፡፡
5)የብልት ሽፍታ
በወንድ ወይም በሴት ብልት እንዲሁም መቀመጫ አካባቢ የሚወጣ ሽፍታ ምቾት የሚነሳ ነው፡፡ ፈንገስ፣ በተባይ መወረር ወይም ሌላ አይነት የቆዳ ችግር በማንኛውም የሰውነታችን ክፍል ላይ ቢታይ በፍጥነት ሀኪም ብናማክር መፍትሄ አግኝተን ችግሩ ሊቆም ይችላል፡፡
6)መጥፎ የአፍ ጠረን
ሁሉም ሰው መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳለውና እንደሌለው ማወቅ ይፈልጋል፡፡ የህክምና ባለሙያው ጭምብል አጥልቆ እንኳ ዘልቆ የሚሰማ የአፍ ጠረን ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ የአንዳንድ ሰዎች የአፍ ጠረን ደግሞ ከሌሎች ይበልጥ አስከፊው ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ባክቴሪ የሚከማችበትን ምላስ በመፋቅ ወይም በመቦረሽ ችግሩን ለማቅለል ይቻላል፡፡

ምንጭ፡ አፍሮዶክተርስ

Advertisement