ቆዳችን ስለ ጉበታችን ጤና ይናገራል – The Health Of Our Skin Could Tell us About our Liver Status.

                                                    

ጉበት በሰውነታችን ውስጥ ስራ ከሚበዛባቸው ክፍሎች አንዱ ሲሆን ከተመገብናቸውና ከጠጣናቸው ነገሮች ውስጥ ጎጂና አሲዳማ የሆኑትን ንጥረ-ነገሮች ያጣራል፡፡ በደም ውስጥ አስፈላጊ የሆኑትን ፕሮቲኖችና ሆርሞኖች ያመርታል፡፡ በጥቅሉ ከ500 በላይ ስራዎችን ያከናውናል፡፡ ጉበት በተወሰነ መልኩ ቢቆረጥ ራሱን መልሶ የመተካት ችሎታ ያለው ብቸኛ የአካል ክፍል በመሆኑ አንድ ሰው ከጉበቱ ላይ የተወሰነ ከፍሎ ለሌላ ሰው መለገስ ይችላል፡፡ ጉበት በእያንዳንዷ ደቂቃ ህዋሳቶቻችን የሚፈልጉትን እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ወደእነዚህ ህዋሳት የሚያልፈውን ሂደት በንቃት ይቆጣጠራል፡፡ ታዲያ ጉበት እነዚህን እጅግ አስፈላጊ ተግባራት ማከናወን ሲያቅተውና በተለያዩ ችግሮች ተጠቅቶ ስራውን ሲያቆም በጉበት መጣራት ያለባቸው አላስፈላጊ ነገሮች በሌላ መልኩ መወገድ ይጀምራሉ፡፡ እነዚህ መንገዶች ደግሞ ትክክለኛ ስለማይሆኑ በቆዳ ላይ የሚተዉት ምልክት አላቸው፡፡ በውስጠኛው የቆዳ ሽፋን ላይ የሚጠራቀሙት አሲዳማ ንጥረ-ነገሮች ቀስ በቀስ በላይኛው የቆዳ ገጽ ላይ ትንንሽ እብጠቶችንና ሽፍታዎችን ያስከትላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ቡናማ ቀለም ያለው ነጠብጣብ በማስከተል የእርጅና ምልክት እንዲያላብሰን ሲያደርጉ የሚያሳክኩ ቀያይ ነጠብጣቦችና የቆዳ መሸብሸብ ምልክቶች ይከሰታሉ፡፡ በርግጥ ሁሉም የቆዳ ላይ ችግሮች የጉበት ችግር ምልክቶች ሊሆኑ ባይችሉም ብዙ ሰዎች የጉበት ችግር በቆዳ ላይ ሊታይ እንደሚችል ልብ አንልም፡፡ አንዳንዶቹ የጉበት ህመሞች በፊትና በጉንጭ ላይ እንዲሁም በአፍንጫ አካባቢ ቀያይ ምልክቶችን ይተዋሉ፡፡ የቆዳ ህክምና ባለሞያዎች ለተለያዩ የቆዳ ህመሞች የተለያዩ መድሃኒቶችን ያዛሉ፡፡ ከሁሉም በፊት ግን የጉበት ምርመራ ማድረግ ችግሩን በአቋራጭ ሊቀርፍ ስለሚችል ጉበት ጤነኛ መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ነው ይላልliverdoctor.com በፅሁፉ፡፡
ምንጭ፦ liverdoctor.com

Advertisement