በኦፕሬሽን መውለድ ጥቅሙና ጉዳቱ – Birth (C-Section and Normal Delivery)

                                                   

(በሰብለወንጌል አይናለም)
ህጻናት ይህችን ዓለም በሁለት መንገድ ይቀላቀላሉ፡­ በምጥ ወይም ደግሞ በኦፕሬሽን (surgical delivery by Caesarean section)፡፡ በአሁን ወቅት የህክምና አማራጭ ያላቸው እናቶች አምጦ ከመውለድ ይልቅ በኦፕሬሽን መውለድን እንደተሻለ አማራጭ ሲወስዱት ይታያል፡፡ አንዳንድ የህክምና ባለሙያዎችም በሁለቱም መንገድ መውለድ ያለውን ጠቀሜታና የጎንዮሽ ጉዳት አስረድተው ውሳኔውን ለእናቶች ከመተው ይልቅ በኦፕሬሽን እንዲወልዱ እናቶችን ሲገፋፉ ይታያል፡፡ ለመሆኑ በኦፕሬሽን መውለድ መቼ መፈቀድ አለበት? ያለው ጥቅምና ጉዳቱስ ምንድን ነው?
በኦፕሬሽን መውለድ መቼ መወሰን አለበት?
1. አምጦ መውለዱ ለእናትየው ወይም ደግሞ ለህፃኑ ህይወት አደጋ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ሲታመንበት
2. ጽንሱ በጣም የፋፋ/የወፈረ/ ከሆነ እና የእናትየው ማህጸን ጠባብ ከሆነ 
3. የጽንሱ አቀማመጥ በትክክል ካልሆነ ማለትም በእርግዝና የመጨረሻዎች ቀናት ጭንቅላቱ ወደታች ካልመጣ 
4. በምጥ ወቅት ጽንሱ በቂ ኦክስጅን ካላገኘና የመተንፈስ ችግር ካጋጠመው 
5. መንታና ከዚያ በላይ ጽንስ ሲኖር 
6. የተራዘመ ምጥ ሲኖር እና 
7. እናትየው ከፍተኛ የደም ግፊት ካለባት፤ የስኳር በሽተኛ ከሆነች፡ የHIV ቫይረስ ካለባት

ጥቅሙ፡­

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ እናቶችን እና የጽንስን ህይወት ይታደጋል፡፡ እናቶች በምጥ ወቅት ሊሰማቸው የሚችለውን የተራዘመ ስቃይ ያስቀራል

ጉዳቱ፡­

1. ጽንሱን ለማውጣት የሚቀደደው የሰውነት ከፍል ለመዳን ጊዜ ይወስዳል፤ በሰውነት ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳም በቀላሉ የሚድን አይደለም
2. የእናቶችን የሆስፒታል ቆይታ ያራዝማል፡፡ በኦፕሬሽን የሚወልዱ እናቶች በፍጥነት አገግመው ልጆቻቸውን ለማጥባትም ሆነ ለመንከባከብ ይቸገራሉ
3. የመጀመሪያ ልጃቸውን በኦፕሬሽን የወለዱ እናቶች ቀጣይ ልጆችን በተመሳሳይ ሂደት እንዲወልዱ ሊገደዱ ይችላሉ፡፡ ይህም በማህጸን ግድግዳ ላይ ተደጋጋሚ ጠባሳዎች ያስከትላል፤ ቁስሉ በቶሎ ካልዳነ ደግሞ የማህጸን ግድግዳ ከሌላ የሰውነት ከፍል ጋር ሊጣበቅ ይችላል 
4. በምጥ ከሚወልዱ እናቶች ይልቅ በኦፕሬሽን የሚወልዱ እናቶች ለከፍተኛ ደም መፍሰስና እንፌክሽን ይጋለጣሉ፡፡ በኦፕሬሽን የሚወልዱ እናቶች በምጥ ከሚወልዱ እናቶች የመሞት ዕድላቸው ሶስት አጥፍ የሰፋ ነው
5. በኦፕሬሽን ሂደት ውስጥ የሽንትና የሰገራ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ሊጎዱ ይችላሉ
ስለዚህ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር እናቶች አምጠው መውለድን ቢመርጡ ይመከራል፡፡ አምጠው የሚወልዱ እናቶችም የተሻለ የመንፈስ እርካታ እንዳለቸው ይናገራሉ፡፡

ምንጭ፡- ጤና

Advertisement