ደስተኛ ለመሆን ትፈልጋላችሁ? እነዚህን 20 አመለካከቶች ቀይሩ::

                        

ደስተኛ ሰዎች እያንዳንዱ እርምጃቸው ላይ በራስ መተማመን ይታያል፡፡ የሚናገሩትን ነገር የሚያደርጉት ይመስላል፡፡ የትኛውም ስፍራ ሲገኙ ዙሪያ ገባውን በአስደሳች ስሜት መሙላት ያውቁበታል፡፡ ደስተኛ ሰዎች ህይወትን በደስታ እያጣጣሙ መኖር የሚችሉበትን ምስጢር የደረሱበት ይመስላል፡፡
የእነዚህ ሰዎች ደስታ ምስጢር በአመዛኙ ከአንዳንድ አይነት ልማድ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ‹‹ይሄ ብቻ ነው ልክ ብሎ›› ሙሉ እውቅና የሰጠውን ነገር እነርሱ ሌላ ልክ ነው ወይም የተሻለ ነው ብለው በሚያስቡት ልምድ የመተካት ዝንባሌ ይታይባቸዋል፡፡ ደስተኛ ሰዎች ደስተኛ ለመሆን ወደ ውጪ አይመለከቱም፡፡ ይልቁንም የውስጥ መሪ ኮምፓሳቸው ላይ እምነት ይጥላሉ፡፡

ደስታ ኮትኩተው ሊያሳድጉት የሚችሉት ነገር ነው፡፡ እናም ማህበረሰቡ ልክ ናቸው ብሎ ያጠመቀንን ልማዶች በገዛ ራሳችን የውስጥ ምሪት በተገኙ ልማዶች በምንተካበት ልክ ደስተኛ እንሆናለን፡፡
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት 20 አመለካከቶች ኑሮ የሚባል ትምህርት ቤት ውስጥ ቀስመናቸዋል የምንላቸው ነገር ግን መለወጥ የሚገባቸው የህይወት አተያዮች ናቸው፡፡ መቀየር የሚጠበቅብንን እነዚህን አመለካከቶች እስኪ አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡፡

1. አንድ ነገር የሚሰራበት ልክ እና ስህተት የሆነ መንገድ አለ፡፡
አዳዲስ ነገሮችን መሞከር እና የተለዩ ሂደቶችን መፈተሽ የዕድገት አካል ነው፡፡ ለአንድ ሰው የሚሰራ ነገር ለአንተ/ለአንቺ አይሰራ ይሆናል፡፡ የራሳችሁን እምነት እና የራሳችሁን ሂደት ፈልጉ እና እርሱን ተከተሉ፡፡ ሌሎችም እንዲሁ የራሳቸውን ፈልገው ይከተሉ፡፡
2. ሌሎችን መምሰል ህብረት መፍጠር ነው፡፡ ሌሎችን ለመምሰል ስንሞክር የራሳችን የውስጥ ፍላጎት ላይ እስር እናውጃለን፡፡ ሌሎችን ለመምሰል መሞከር ለራስ ታማኝ አለመሆን ነው፡፡ ሌሎችን ለመምሰል ከመጣር ይልቅ ከገዛ የውስጥ እና የእውነት ማንነታችን ጋር ለመሰለፍ፣ በአንድነት ለመቆም ጥረት ማድረግ ይበልጣል፡፡ በራሳችሁ መተማመን ስትጀምሩ እና በራሳችሁ ደስተኛ ስትሆኑ ከሌሎች ጋርም ራሳችሁን ሳታጡ የላቀ ግንኙነት እና ትብብር መፍጠር ትችላላችሁ፡፡
3. ጠንክሮ መስራት ስኬታማ ያደርጋል፡፡ ከልክ በላይ ትዝላላችሁ፡፡ በጥረታችሁ ያን ያህል አትደሰቱም፡፡ በጥንካሬ በመስራት ምትክ በብልሃት እንዴት መስራት እንደምትችሉ አስቡ፡፡ ስኬታችሁን በምታገኙት ደስታ መጠን መዝኑ፡፡
4. ውድቀት ክፉ ነገር ነው፡፡ መውደቅ ስለራሳችሁ ድንቅ ትምህርት የምትቀስሙበት መንገድ ነው፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ሞክረን ሳይሳካልን ሲቀር ለምን ሊሳካልን እንዳልቻለ እና በቀጣይ ደግሞ ምን ምን ብናደርግ ስኬታማ መሆን እንደምንችል እንማራለን፡፡ አለማችን ላይ እጅግ በጣም የተሳካላቸው ሰዎች ብዙዎቹ ብዙ ጊዜ ወድቀው የተነሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፡፡ ‹‹በቂ ውድቀት ውድቄያለሁ ወይ?››
5. ብቻችሁን ሆናችሁ ማለት ብቸኛ እንደሆናችሁ ትዘልቃላችሁ ማለት ነው፡፡ ከራሳችሁ ጋር በምትኑበት ወቅት ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ የምትችሉ ከሆነ ብቻችሁን የምትሆኑበት ጊዜ ያለ ምንም ጥርጥር መጠኑ እያነሰ ይመጣል፡፡
6. ህይወት አልጋ በአልጋ መሆን አለበት፡፡ የህይወት ከፍታና ዝቅታዎች ሚዛናዊ ህይወት የምንኖርበት መንገድ ነው፡፡ እያንዳንዱን ሂደት በፀጋ ተቀበሉ፡፡ ግብግብ መግጠማችሁን ስትተዉ ሰላም ማግኘት ትጀምራላችሁ፡፡
7. ሰዎች ስለ እናንተ የሚያስቡት ነገር ወሳኝ ነው፡፡
ዋናው እጅግ በጣም ወሳኙ ነገር እናንተ ስለ እናንተ የምታስቡት ነው፡፡ ከራሳችሁ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ላይ ስሩ፡፡ ከአሰባችሁት በላይ ደስታ እና ፍቅር ይሰማችኋል፡፡
8. ቀጭን፣ ቆንጆ፣ ብልጥ፣ ሀብታም፣ ጤነኛ ብትኑ ኖሮ ደስተኛ ትሆኑ ነበር፡፡
ከእናንተ ቁጥጥር ውጪ ያለ ነገር ላይ ደርሳችሁ ደስተኛ እንሆናለን ብሎ ማሰብ ከንቱ ድካም ነው፡፡ የምትፈልጉት የክብደት መጠን፣ የምትፈልጉት አይነት አፍቃሪ ግንኙነት፣ ፍፁም ለእናንተ የሚስማማ ስራ አግኝታችሁ ይሁን እንጂ ደስተኛ መሆን ያልቻላችሁት ምን ያህል ጊዜ ነው? ሁልጊዜ! ደስታ ከእኛ ውጪ የሚገኝ ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንም እውስጣችን የሚገኝ ፈርጥ ነው፡፡
9. ህይወታችሁ ከመንገድ ዝንፍ ብሎ ወጥቷል፡፡
‹‹መድረስ ያለብኝ ቦታ አይደለም የደረስኩት›› አልያም ደግሞ ‹‹ህይወቴን እንደ አሰብኩት አይደለም እየመራሁ የምገኘው›› የሚል ሃሳብ ዛሬን በደስታ እንዳታሳልፉ እንቅፋት ይሆንባችኋል፡፡ የምትፈልጉት ቦታ ነው ያላችሁት፡፡ ሁሉም ነገር ያለ ምንም መዛነፍ እንደሚከናወን እመኑ፡፡
10. መተው መሸነፍ ነው፡፡
ወደ ታች የሚጎትታችሁን ነገር መተው ስኬት እና ደስታ የምታገኙበት አንድ አዲስ መንገድ ነው፡፡ ጥቅም እየሰጣችሁ ያልሆነን ነገር ስትተዉ ከልብ የምትፈልጉት ነገር ወደ ህይወታችሁ እንዲገባ በራችሁን ወለል አድርጋችሁ ከፈታችሁ ማለት ነው፡፡ ‹‹መተው ነገሬን ከተተው›› አደል ከነተረቱስ?
11. አልሆን ያለን ነገር መጠበቅ ጥሩ ነው፡፡
ከአዲስ እና እንግዳ ዓለም ጋር በስምምነት መኖርን እወቁበት፡፡ አልሳካ ያሉ ነገሮች ላይ እንዲሁ የማናውቀውን መልዓክ ስለፈራን ብቻ የምናውቀው ሰይጣን ላይ ተጣብቀን መኖር የለብንም፡፡
12. ደስታን ለነገ፣ ለነገ ወዲያ ይደርስበታል ብሎ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡
ጡረታ፣ የዓመት ረፍት፣ ቅዳሜ እና እሁድ ወዘተ… የምንላቸው ነገሮች በአሁኑ ሰዓት ደስታን ለአለማጣጣም በምክንያትነት የምንደረድራቸው ሰበቦች ናቸው፡፡ እያንዳንዱን ቀን በደስታ ለማሳለፍ ሞክሩ፡፡
13. ከልባችሁ ይልቅ ጭንቅላታችሁን መስማት አለባችሁ፡፡
ጭንቅላታችሁ አንዳንዴ ልክ እንደሆነ ከሚሰማችሁ ነገር ውስጥ ጎትቶ ያወጣችኋል፡፡ የልባችሁን ምሪት መከተል ስህተት አይደለም፡፡ ያላችሁበት የትኛውም አይነት ሁኔታ ልክ እንደሆነ ይሰማችሁ እንደሆነ ራሳችሁን ጠይቁ፡፡

14. እንዴት እውን እንደምታደርጉት/እንደምታሳኩት ያላወቃችሁትን ነገር አትሞክሩ፡፡
ህልማችንን እንዴት ማሳካት እንደምንችል እግረ መንገዳችንን እንማራለን፡፡ ስለዚህ ሞክሩት፡፡ የወደፊቱ ማንነታችሁ (Future self) ያመሰግናችኋል፡፡
15. የማይተባበሯችሁ ሰዎች ስለ እናንተ ግድ የላቸውም፡፡
ሌሎች የሚናገሩት እና የሚሰሩት ነገር ከእናንተ ጋር ምንም የሚያያይዘው ነገር የለም፡፡ ይበልጥ በራሳችሁ እና በህልማችሁ መተማመን በጀመራችሁ መጠን ያን ያህል ሌሎች አመኑባችሁ አላመኑባችሁ ግድ አይሰጣችሁም፡፡
16. ራስን መውደድ ስህተት ነው፡፡
ለራሳችሁ መቆም ስትችሉ ነው ለቀሪው ዓለምም መቆም የምትችሉት፡፡ ሁሌም ቢሆን ፍቅርን ከራሳችሁ እንደጀመራችሁ እርግጠኛ ሁኑ፡፡ ሙሉ ነገር ነው ለሌላውም የሚተርፈው፡፡
17. ህልማችሁን ወደ ጎን ተወት አድርጋችሁ ኃላፊነታችሁን መወጣት አለባችሁ፡፡
ህልማችሁ ኃላፊነታችሁ ነው፡፡ በመሆኑም በረባ ባልረባ ሰበባ ሰበብ የነፍስ ጥሪያችሁን ቸል አትበሉ፡፡
18. መዳረሻው ነው ሽልማቱ፡፡
መድረስ የሚባል ነገር የለም፤ ሂደቱ እና ጉዞው ነው ሽልማቱ፡፡ ስለዚህ እመንገዳችሁ ላይ ሃሳባችሁን ሰብስባችሁ መገኘታችሁን አረጋግጡ፡፡
19. ምስጢርን ማካፈል የድክመት ምልክት ነው፡፡
የውስጥ ስሜታችሁን እና ሃሳባችሁን ለሌሎች ማካፈል ደስተኛ መሆን የምትችሉበት ምስጢር ነው፡፡ ስሜታችሁን ማካፈል ማለት ግልፅ መሆን እና ነገሮችን ለመሸፋፈን አለመጣጣር ማለት ነው፡፡ ግልፅነት አሁን የምትገኙበትን ማንኛውም አይነት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ መቀበል እና በኩራት ይህንን ማንነት ማንፀባረቅ ስራችሁ ነው፡፡
20. ማንነታችሁ ስራችሁ ነው፡፡
እናንተ ተውላጠ ስም አይደላችሁም፡፡ ከስራችሁ እና ከለት ተለት እንቅስቃሴያችሁ በላይ እጅግ የላቃችሁ ናችሁ፡፡ ሁሉን ነገር ማንነትንም ጨምሮ ከሥራ ጋር ማያያዝ ተገቢ አይደለም፡፡ ሥራችሁ የማንነታችሁ አንድ አካል እንጂ ማንነታችሁ አይደለም፡፡

Advertisement