የልጅ የማሳደግ ኀላፊነት

                                                      

ልጆች ከእግዚአብሔር ዘንድ ለወላጆች የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው። ወላጆችም ልጆችን እግዚአብሔር በሚፈልገው መልኩና መንገድ ያሳድጉ ዘንድ ትልቅ ኀላፊነት ተሰጥቶአቸዋል። ወላጆች የልጆችን የአሁኑን እና መፃኢ ሕይወታቸውን የመቅረፅ ወርቃማ ዕድል የተሰጣቸው የማኅበረ ሰቡ አንኳር አካል ናቸው። ከመፀነስ ጀምሮ ያለው የልጆች ዕድሜ ወላጆች እንደ እግዚአብሔር ቃል ልጆች ላይ መልካም ዘርን ይዘሩ ዘንድ ምቹ የሆነ አጋጣሚን ይፈጥራል።

የልጅ አሳዳጊነት ጉዳይ ትኩረት የሚሻና በጥልቅ ሊዳሰስ የሚገባው ጉዳይ ነው። ይህ ጽሑፍ በዋናነት የሚያተኩረው በወላጅነት ላይ ሲሆን፣ የወላጅ ኀላፊነት በልጆች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ፣ የመልካም ወላጅነት ገጽታን፣ የወላጅነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መለኪያን እንዲሁም መልካም የልጆች አስተዳደር አግባብነት ያለው ወላጅነትን ለአንባብያን ለማስገንዘብ አልሟል።

የወላጅነት ትርጉም

ወላጅነትን ስንተረጉም “ቤተ ሰብ” የሚለውን ቃል አጽንኦት ልንሰጠው ይገባል። “ቤተ ሰብ” የሚለውን ቃል ለመግለጽ የተለያዩ ፍቺዎች ተሠጥተዋል። እነዚህም፡-

  • “ቤተ ሰብ ከእናትና ከአባት እንዲሁም ከልጆች የተዋቀረ ቡድን ነው።” (Webster Dictionary)
  • “ቤተ ሰብ በማኅበረ ሰብ ውስጥ ልጆችን የሚያሳድግና የሚያስተምር ተቋም ነው። የማኅበረ ሰብም ሥረ መሠረት ተደርጎም ይቆጠራል።” (Wyse, 2000)
  • “ቤተ ሰብ የኅብረተ ሰብ የተፈጥሮ መሠረታዊ መነሻ ነው። ከኅብረተ ሰብና ከመንግሥት ጥበቃ የማግኘት መብት አለው።” (የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34/3)።

ከላይ ስለ ቤተ ሰብ የተሰጡት ፍቺዎች በቤተ ሰብ ውስጥ ወላጆች የተባሉ በቁጥር ሁለት የሆኑ ተቃራኒ ጾታዎች ለቀሪው የቤተ ሰብ አካል በኀላፊነት እንደተቀመጡ ያስረዳሉ። በመሆኑም ወላጅነት ማለት የቤተ ሰብ ኀላፊነትን በአግባቡ መወጣት ማለት ነው። ወላጅነት ልጆችን የማሳደግ ጥበብ/ክኅሎት የሚጠይቅ ሥራ ማለትም ጭምር ነው። ወላጅነት ልጆች ከሚፀነሱበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ ውስብስብ የሆነና አወንታዊ ተጽእኖ ለማምጣት ብዙ ጥረትን የሚጠይቅ ተግባር ነው።

የልጅ አስተዳደግ ዘይቤዎች

ልጆችን የማሳደግ ተግባር የተመሠረተው በወላጆችና በልጆች መካከል በሚፈጠረው ሥነ ፍጥረታዊ ቁርኝትና መስተጋብር ላይ ነው። የልጅ አስተዳደግ ዘይቤዎችም እንደ የወላጅ አያያዝና አቀራረብ የተለያዩ ናቸው። የልጅ አስተዳደግ ዘይቤ በውስጡ ሁለት መሠረታዊ መነሻዎችን ያካትታል። እነሱም፡- የወላጆች ምላሽ ሰጪነት (ለልጆች የሚገባውን ትኩረትና ለጥያቄዎቻቸውም አግባብነት ያለው ምላሽ መስጠት) እና የወላጅ ፍላጎት አነሣሽነት (የልጆችን ፍላጎትና ጥያቄ ማወቅ) ናቸው። የሁለቱ ፅንስ ሐሳቦች መስተጋብር የልጅ አስተዳደግ ዘይቤን ይፈጥራል። ለልጆች የሚገባውን ትኩረትና ለጥያቄዎቻቸው አግባብነት ያለው መልስ የሚሰጡ ወላጆች እንዳሉ ሁሉ ልጆች ምንም እንደማያውቁና የተነገራቸውን ብቻ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚያስቡና ለልጆች ጊዜና ፍላጎት ቦታ የማይሰጡ ወላጆችም አሉ።

የልጅ አስተዳደግ ዘይቤዎች

  1. አዛዣዊ (Authoritative)

ይህ የልጅ አስተዳደግ ዘይቤ በራስ መተማመንን ያበረታታል፤ ተቀባይነት ያለው ገደብን ያበጃል፤ አነቃቂና አበረታች ነው። በቂ የቃላት ማብራሪያና ውይይትን ይጠቀማል፤ አዎንታዊ ስሜትና ቃላትን አዘውትሮ ይናገራል። በመሆኑም ይህ የልጅ አስተዳደግ ዘይቤ በሁለንተናቸው ውጤታማ የሆኑ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ለራሳቸውና ለሌሎች ስሜት የሚጠነቀቁ ልጆች የሚቀረጹበት መንገድ ነው። (Dehart 2000, Berk, 1999)

  1. ፈላጭ ቆራጭ (Authoritarian)

ፈላጭ ቆራጭ የልጅ አስተዳደግ ዘይቤ ደንብና መመሪያን አብዝቶ ይጠቀማል፤ ገደብ ማበጀትን ያበዛል፤ ቅጣትን (ዛቻ እና ድብደባ) ያዘወትራል፤ የፍቅርና የጨዋታ ስሜትን አያሳይም፤ እንዲሁም ከቃላት ማብራሪያ ይልቅ የጽሑፍ መመሪያን ይመርጣል። በዚህ የልጅ አስተዳደግ ሥርዐት የሚያልፉ ልጆች መመሪያን አጥብቀው የሚከተሉ፣ ሥልጣንን የሚያከብሩ እና ሥራ ወይም ጥረት ላይ የሚያተኩሩ እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል። ፈላጭ ቆራጭ የልጅ አስተዳደግ ማኅበራዊ ግንኙነታቸው ደካማ የሆኑ፣ የሚጨነቁ፣ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው፣ የፈጠራ ችሎታቸው የከሰመ እና ዝቅተኛ የመግባባት ችሎታ ያላቸው ልጆች እንዲሆኑ የማድረግ አደጋ አለው። (ዝኒ ከማሁ)

  1. ልል (Permissive)

በዚህ የልጅ አስተዳደግ ዘይቤ ውስጥ ወላጆች አነስተኛ የሆነ መመሪያን ይሰጣሉ፤ ልጆችን በቅርበት የመከታተል ዝንባሌ ያላቸውና ልጆች የሚወዱትን ሁሉ እንዲያደርጉ የሚፈቅዱ ናቸው። ለልጆቻቸውም እጅግ የበዛ የፍቅርና የስሜት ምላሽ ያሳያሉ። በተጨማሪም፣ ለልጆች የሚደረገው አካላዊ ቅርርቡና እርዳታው የበዛ ቢሆንም ግልጽ የሆነ መመሪያ ግን የላቸውም። የልል ልጅ አስተዳደግ ዘይቤ በልጆች ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ በግልጽ የሚታይ ነው። በሌሎች ላይ ጥገኛ የሆኑ ልጆች፣ እራሳቸውን የማይቆጣጠሩ፣ በራሳቸው የማይተማመኑ እና ውጤታማ ያልሆኑ ልጆች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል። (ዝኒ ከማሁ)

  1. ቸልተኛ (Uninvolved)

ይህ የልጅ አስተዳደግ ዘይቤ በልጆች ሕይወት ውስጥ የማይገባና ግድ የሌለው ሲሆን፣ የስሜትና የቃላት ምላሽ የማያሳይና መመሪያ የማያውቀው ነው። ውጤቱም ያልተሳካላቸው፣ እራሳቸውን የማይቆጣጠሩ፣ ፍቅርን የሚፈልጉ፣ ኀላፊነት የማይሰማቸው ልጆች እንዲሆኑ በር ይከፍታል።

መልካም ወላጅነት

የተለያዩ የልጅ አስተዳደግ ዘይቤዎች የልጆችን የአሁንና የወደፊት ሕይወት ከመቅረፅ አኳያ የራሳቸው የሆነ ጥቅምና ጉዳት አላቸው። በአብዛኛው ጊዜ እነዚህ የአስተዳደግ ዘይቤዎች ሚዛኑን ጠብቀው ሲጓዙ አይታይም፤ ቸልተኛ ወይም እጅግ በጣም ጥብቅ ይሆናሉ፤ አሊያም ሲበዛ መረን የለቀቀ ይሆናል። መልካም ወላጅነት እጅግ በጣም ጥብቅና መረን የለቀቀ አይደለም። ይልቁንም ሚዛኑን የጠበቀና ያልተዛባ የልጅ አስተዳደግን ይከተላል።

መልካም ወላጅነት ልጆች ሊኖሩ በሚገባቸው ትክክለኛ ቦታ ላይ እንዲቀመጡ ያደርጋቸዋል። ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው (መዝሙረ ዳዊት 127፥3)። በመሆኑም ተገቢውን ክብር፣ ፍቅር እና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል። መልካም ወላጅነት ልጆች ለዕድገት ምቹና ተስማሚ በሆነ አካባቢ እንዲያድጉና እግዚአብሔር የሰጣቸውን ዕምቅ ችሎታ አውጥተው እንዲጠቀሙበት ያደርጋል።

የመልካም ወላጅነት መገለጫዎች

  1. ተሳትፎ

ወላጆች በልጆች የሕይወት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይመከራል። ልጆች ዋጋ እንዳላቸውና ጠቃሚ እንደሆኑ ማስተማርንም ያካትታል። በተጨማሪም፣ ወላጆች የልጆች አማካሪ ሆነው በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጊዜ ሳይቀር ከጎናቸው እንዲቆሙ ይመከራል።

  1. ማበረታታት

የምስጋና እና የአድናቆት ቃላት ልጆች ለራሳቸው የተሻለ ግምት እንዲሰጡ ያደርጋል። ልጆች ጥሩ ነገሮችን ሲያከናውኑ ወላጆች ጊዜ ሰጥተው ሊያበረታቷቸው ይገባል።

  1. ጥንቃቄ የተሞላበት ክትትል ማድረግ

ልጆች የት እንደሚውሉ፣ ጓደኞቻቸው እነማን እንደሆኑ፣ በትምህርት ቤት ያላቸው ብቃት፣ የሚጠሉትንና የሚወዱትን ማወቅና መከታተል ይጠይቃል። ይህም ወላጆች በልጆቻቸው ሕይወት ውስጥ ትክክለኛ የሕይወት አቅጣጫን እንዲይዙና እንዲያርሟቸው ያግዛል።

  1. አግባብነት ያለው ቅጣት

ቅጣቱ ቤተ ሰቡ አስቀድሞ ባወጣቸው መመሪያዎች ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን፣ ልጆች ሲያጠፉ እርማት መስጠት የሚለውን እንደ መርሕ ይይዛል። ዋና ዓላማው ደግሞ በቀል ሳይሆን የመታረም ፅንስ ሐሳብን ማጉላት ነው፤ የሚፈጸሙት ቅጣቶችም ልጆችን ከስሕትታቸው እንዲታረሙ የሚያስችል መሆን አለበት።

  1. መፍትሔ ሰጪነት

ልጆች ሲያድጉ በራሳቸው ለችግሮቻቸው መፍትሔ መስጠትን መማር አለባቸው። በመሆኑም ወላጆች ለችግሮቻቸው የሚሰጡት መፍትሐ በልጆች ላይ ተቀባይነትን የሚፈጥርና አሳማኝ ሊሆን ይገባዋል። ወላጆች በሕይወት ውስጥ ሊመጡ ያሉትን ተግዳሮቶች ቀድሞው ማወቅና እግረ መንገዳቸውንም በጊዜ ፍቱን ምላሽ ሊሰጡት ይገባል።

ምንጭ :- ሕንጸት

Advertisement