የአለም አቀፍ የቡና ቀንና ኢትዮጵያ

                                                                

ቡና ከማሳ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው እስኪደርስ ድረስ ያለውን ሂደት ማሰየትና ተወዳጅ የሆነውን ቡና አምራች የሆኑትን በአነስተኛ ማሳ ላይ የተመሰረቱ አምራቾችን ተገቢውን ክብር በመስጠት ዕለቱ እንደሚከበር በምህጻረ ቃል (ICO) የአለም አቀፉ ቡና ድርጅት ገልጿል፡፡

በየአመቱ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጥቅምት 1 የሚከበረው አለም አቀፉ የቡና ቀን 77 አገራትን በአባልነት ባቀፈው የአለም አቀፉ የቡና ድርጅት አስተባባሪነት ይከበራል፡፡

ባለፉት 50 ዓመታት የቡና በምርታማነትም ሆነ በፍጆታ ረገድ ዕድገት ማሳየቱን የአለም አቀፉ የምግብ ድርጅት (FAO) መረጃ ያመለክታል፡፡ ቡና በ70 ሀገራት ብቻ የሚመረት ሲሆን ብራዚል፣ ቬትናምና ኢንዲኖዥያ የጠቅላላ ሀገራት ምርትን 50 በመቶ ድርሻ ይይዛሉ፡፡

የቡና ንግድ በምርቱ አቅርቦትና ጥራት ላይ ይወሰናል፡፡ የቡና አይነት አረቢካ ወይም ሮቦስታ መሆኑ፣ በቡናው ውስጥ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ መኖሩና ያለመኖሩ፣ የታጠበና ያልታጠበ መሆኑ እንዲሁም እሴት የተጨመረበትና ያልተጨመረበት መሆኑ በገበያው ላይ የራሱ ድርሻ አለው፡፡

የቡና ምርትን በተለይም ለታዳጊ ሀገራት ዋንኛው የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙበት ዘርፍ ነው፡፡ ቡና ላኪ ሀገራት በ2012 ወደ ውጭ ከላኩት 70 ሚልዮን ኩንታል የቡና ምርት 24 ቢልዮን ዶላር ማግኘት መቻላቸውን የአለም ምግብ ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡ አኃዙ ከአስር አመታት በፊት ከነበረው አንጻር በምርት 25 በመቶ እና በውጭ ምንዛሪ ግኝት በ3 ዕጥፍ መላቁን ከተመሳሳይ ምንጭ የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡ በአለም ደረጃ ሁለት አይነት የቡና ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡

አረቢካና ሮቡስታ በመባል ይታወቃሉ፡፡ የቡና ዝርያዎቹ እንደየ ቅደም ተከላቸው 40 እና 60 በመቶ የአለም አቀፉን የቡና ጠቅላላ ምርት ድርሻን ይዛሉ፡፡ የአረቢካ የቡና ዝርያ በዋጋ ረገድ ከሮቡስታ የተሻለ ቢሆንም ከ2013 ወዲህ የሮቡስታ ቡና ምርት መጨመሩን ተከትሎ የአሪቢካ ቡና ዋጋ እያሽቆለቆለ መምጣቱን የአለም ምግብ ድርጅ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ የቡና፤ ምርትና ፍጆታ የቡና መገኛ እንደሆነች የምትታመነው ኢትዮጵያ በቡና ምርት በአፍሪካ ቀዳሚ ነች። በአለም ደግሞ 5 ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የሀገሪቱ የቡና ምርት የአለምን 5 በመቶ የአፍሪካን ደግሞ 39 በመቶ ድረሻ እንደያዘ የአለም ቡና ድርጅት (ICO) መረጃ ያመለክታል፡፡ በኢትዮጵያ በቡና የተሸፈነው መሬት ለቡና አመቺ ከሆነው አንጻር በጣም አነስተኛ ነው፡፡

በቡና የተሸፈነው መሬት መጠን ግማሽ ሚልዮን ሄክታር ገደማ ነው፡፡ የተሸፈነው መሬት ለቡና ምርት ምቹ ከሆነው 6 ሚልዮን ሄክታር አንጻር 3.8 በመቶ ብቻ ይሸፍናል (Mekuria.et)፡፡ ኢትዮጵያ በቡና ምርት ዕድገት መጠን ከአለም ቀደሚዋ ናት፡፡

ምርቱ በየአመቱ 12 በመቶ በማስመዝገብ የአለምን የቡና ምርት ዕድገት መጠንን ይመራል፡፡ ብራዚል፣ ቬትናምና ኮሎምቢያ አንደ ቅደም ተከተላቸው 7፣ 5፣ እና 3 በመቶ በማስመዝገብ ኢትዮጵያን እንደሚከተሉ የአለም ምግብ ድርጅት FAO ሪፖርት ያስረዳል፡፡

አብዛኛው የኢትዮጵያ ቡና ምርት አነስኛ ማሳን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ከአንድ ሄክታር በታች በሆነ ማሳ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች የሀገሪቱን ጠቅላላ የቡና ምርት 90 በመቶ ድርሻ እንደሚሸፈኑ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ ያመለክታል፡፡

የተፈጥሮ ደን 5 በመቶ ድርሻ ሲኖረው ቀሪውን ሰፋፊ እርሻን መሰረት ያደረገ የቡና ምርት ይሸፍናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ቡና በማምረት የተሰማራውን 15 ሚልዮን ያህል አርሶ አደር ተጠቃሚ ለማድረግ ከአለም አቀፉ ቡና ድርጅትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በተለይም ዕውቅና ካገኙት የይርጋ ጨፌ፣ ሲዳሞና ሀረር ስፔሻሊቲ ቡናዎች በተጨማሪ ሌሎችንም ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ ቡናን ጨምሮ በሀገሪቱ የሚመረቱ ምርቶች ግብይት ለማሳለጥ በአፍሪካ በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ቡና አምራቹ የለፋበትን ዋጋ እንዲያገኝ ያራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቡና ፍጆታ ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አመታዊ ፍጆታው በነፍስ ወከፍ 2.4 ኪሎ ግራም መሆኑን የአለም አቀፉ ቡና ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡ የጠቅላላ የሀገሪቱ የቡና ምርት ገሚሱ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚዉል ነው፡፡ ከጠቅላላ ምርት አንጻር የሀገሪቱ የቡና ፍጆታ ድርሻ፤ ኢትዮጵያን ከአለም አንጻር ቁጥር አንድ እንደሚያደርጋት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በዘርፉ ያደረገው ጥናት ያመለክታል፡፡

በሌላ ጎኑ የሀገሪቱ ባህላዊ የቡና አፈላል በፍጥነት ወደ ንግድ እየተቀየረ መምጣቱን ተከትሎ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡ የቡና ንግዱ ከትልቅ እስከ ትንሽ የሀገሪቱ ከተማዎች መስፋፋቱ የቡና ፍጆታውን በማሳደግ ረገድ ያራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ወጪ ንግድ የቡና ምርት ኢትዮጵያ ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ነው፡፡ እንደ ማዕከላዊ ስታስቲስክ ኤጀንሲ መረጃ፤ ቡና ሀገሪቱ 31 በመቶ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ምርት ነው፡፡

ከ10 አመት በፊት የቡና ምርት የውጭ ምንዛሪ ግኝት 65 በመቶ ድርሻ እንደነበረው መረጃው ያመለክታል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናን በመላክ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በጎርጎሮሳዊያኑ 1990ዎቹ ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ አንጻር አሁን ያለው በ5 ዕጥፍ ገደማ ይልቃል፡፡ በተለይም ከ2003 ጀምሮ የቡና የአለም ገበያ ዋጋ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ ከቡና የተገኘው ገቢ እያደገ መጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ የቡና ምርት ጥራትን ብቻ በማሳደግ አሁን እየተገኘ ያለውን የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደሚቻል የአለም ምግብ ድርጅት FAO ጥናት ያመልክታል፡፡ ሀገሪቱ ወደ ወጭ የምትልከው ቡና አብዛኛው ያልታጠበ ነው፡፡ ወደ ውጭ ከሚላከው ቡና የታጠበ ቡና 27 በመቶ ብቻ ድርሻን ይዛል፡፡ ቀሪው 73 በመቶ ሳይታጠብ የሚላክ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በአለቀፍ ደረጃ ተወዳጅ የሆነውንና ተፈጥሯዊ (Organic) ቡናን ለአለም ገበያ በማቅረብ ትታወቃለች፡፡ በአለም ገበያ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣውን ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ነጻ የሆነ (Organic) ቡና በከፍተኛ ደረጃ በማቅረብ የምትቀድማት ሀገር ፔሩ ብቻ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ለአለም ገበያ የምታቀርበው ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ነጻ የሆነ ቡና እስከ 20 በመቶ የሚደርስበት ወቅት አለ፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ ከአለም ገበያ ካላት 5 በመቶ ድርሻ አንጻር ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ ይህ ሆኖም ከተፈጥሯዊ (Organic) ቡና የሀገሪቱን ጠቅላላ ኤክስፖርት 6 በመቶ ድርሻን ብቻ እንደሚይዝ የአለም ምግብ ድርጅት FAO መረጃ ያመለክታል፡፡

ከ1990ዎቹ ዓ.ም ወዲህ የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ጀርመን (29 በመቶ) ጃፓን፣ (16 በመቶ) ሳውዲ አረቢያ (15) በመቶ ድርሻን በመያዝ ቀዳሚ ናቸው፡፡ አሜሪካ ከኢትዮጵያ የምትገዛው የቡና መጠን አነስተኛ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ በ1992 ዓ.ም አሜሪካ ከኢትዮጵያ የምታስገባው ቡና 4 በመቶ የነበረ ሲሆን አኃዙ በዕጥፍ በማደግ በአሁኑ ወቅት 8 በመቶ ደርሷል፡፡ በየአመቱ እንደ አውሮፓዉያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 1 የሚከበረው የአለም አቀፍ የቡና ቀን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር የዕለት ዕለት ማህበራዊ ግንኙነታችን ጋር ጥልቅ ትስስር ላለው አረንጓዴ ወርቃችን ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡

ምንጭ:- EBC

Advertisement