“ጆሮና ቀንድ” – ከዳንኤል ክብረት

                                                                   

አንድ ጥጃ የሚያሳድግ ሰው ነበር::ጥጃውን ሲፈልግ ጆሮውን ይጎትተዋል፣ሲፈልግ በዱላ ይዠልጠዋል፣ሲፈልግ ጨው እያላሰ ይስበዋል፣ ሲፈልግ ደግሞ በገመድ አሥሮ ያስከትለዋል፡፡ በዚህ መንገድ ሄዶጥጃው አደገና  ወይፈን ሆኖ ቀንድ አበቀለ የጥጃውም ባለቤት እንደለመደው በዱላ ሊመታው፣ ጆሮውንሊጎትተው፣ በዱላም ሊዠልጠው ተነሣ::ያን ጊዜ ጥጃው አፍንጫውን ወደ መሬት አስነክቶ አኩረፈረፈናእንደ ስፔን በሬ ተወርውሮ በቀንዱ ወጋው፡፡ ሰውየውም ወገቡን ይዞ እየተጎተተ ቤቱ ደረሰ፡፡

ታሞ ሊጠይቁት የሄዱ ጎረቤቱ የሆነው ነገር ሰሙና ‹ወዳጄ የጆሮና የቀንድን ዘመን እንዴት መለየትአቃተህ?› አሉት፡፡ ‹የጆሮና የቀንድ ዘመን ምንድን ነው?› አላቸው ወገቡን አሥሮ እየተገላበጠ፡፡‹በመጀመሪያ የበቀለን ጆሮ በኋላ የመጣ ቀንድ በለጠው› ሲባል አልሰማህም፡፡ ጥጃው መጀመሪያ ጆሮ ብቻስለነበረው ያልከውን ሁሉ ይሰማህ፣ ይታዘዝህ ነበር፤ ብትመታው ይችላል፣ ብትጎትተው ይከተላል፣ብታሥረው ይታሠራል፡፡ ጆሮ ብቻ ስለነበረው መስማት ብቻ ነበር የሚችለው፡፡ በኋላ ግን ቀንድ አበቀለ፡፡ቀንድ ካበቀለ በኋላ እንደ ድሮው እጎትተዋለሁ ብትል አይሆንም፡፡ አሁን ከተስማማው ይቀበልሃል፤ካልተስማማው ግን መዋጋት ይጀምራል፡፡ አሁን አንተ ያደረግከውን ማድረግ የሚቻለው በጆሮ ዘመንነው፡፡ በቀንድ ዘመን እንደዚህ ማድረግ ሞኝነት ነው፡፡

ሁሉም ነገር የጆሮና የቀንድ ዘመን አለው፡፡ በሀገራችን አንድ መንግሥት ሲተከል ሕዝቡ የጆሮ ዘመንይሰጠዋል፡፡ ዝም ይላል፣ ይሰማል፣ ይቀበላል፤ አልጋው እንዲረጋ፣ ዙፋኑ እንደዲጸና ይተጋል፤ ከትናንትዛሬ፣ ከዛሬም ነገ ይሻላል ብሎ በተስፋ ይጠብቃል፡፡ ባያምንም ይቀበላል፤ ባይስማማም ይተባበራል፤ባይግባባም አብሮ ይሠራል፡፡ ይሄ የጆሮ ዘመን ነው፡፡ ብልህ መሪ ከጆሮ ዘመን በኋላ የቀንድ ዘመንእንደሚመጣ ያውቃል፡፡ ስለዚህም ሥርዓት ሠርቶ፣ ሕግ አጽንቶ፣ አገር አልምቶ፣ ሕዝብን አስማምቶይጠብቃል፡፡ በጆሮ ዘመን ያልሠራውን ሥራ በቀንድ ዘመን እሠራለሁ ቢል የሚያምነው የለም፡፡ እንደቀድሞው ዝም ብሎ የሚሰማ፣ አሜን ብሎ የሚቀበል፣ እሺ ብሎ የሚከተል፣ ጎንበስ ብሎ የሚጎተትአይገኝም፡፡ ለተስማማው ጆሮውን ላልተስማማው ቀንዱን ያቀርባል፡፡ ሥራውን በግድ ብተትሠራ እንኳንትግሉ ብዙ ነው፡፡ ሕዝብ ቀንድ ከማብቀሉ በፊት እንደ ቀንዱ ዘመን ማድረግ እንደማይቻለው ሁሉ፣ ቀንድካበቀለ በኋላም እንደ ጆሮው ዘመን ማድረግ አይቻልም፡፡ ራሱ ቀንድ አብቃዩም እንደ ድሮው ልሁን ቢልእሺ አይለውም፡፡ ያላወቁትን እንዳላወቁ፤ ያልሰሙትን እንዳልሰሙ፣ ያላዩትን እንዳላ፣ ያልደረሱበትን እንዳልደረሱ መሆን አይቻልም፡፡ ለውጥን ፈልገህው ብቻ አታመጣውም የቀንድ ዘመን ሲሆን ሳትፈልግም ትለወጣለህ፡፡  

አገር ብቻ ሳይሆን ድርጅት፣ ማኅበር፣ ፓርቲና ተቋምም ቀንድ ያበቅላሉ፡፡ በጆሮ ዘመን አባሉ ሁሉይሰማሃል፤ ትእዛዝ ከበላይ እግር ወደላይ ብሎ ያምናል፡፡ አንድ ቦታ የበሰለውን በልቶ፣ አንድ ቦታየተጠመቀውን ጠጥቶ፣ የተባለውን ሁሉ ሰምቶ፣ ውደድ የተባለውን ወድዶ ጥላ የተባለውን ጠልቶይኖራል፡፡ በአንድ ዓላማ የተመመ፤ በአንድ አቋም የቆመ፤ አንድ ግብ የጨበጠ፤ በአንድ መመሥመርየሠለጠ የሚመስልበት የጆሮ ዘመን አለው፡፡ እንደ አህያ ጆሮ እንደ ጦር ጉሮሮ አንድ ሆኖ ተካክሎየሚታይበት፡፡                              እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ የሚመስልበት ዘመን አለ፤ያኔ አባሉናአካሉ የተግባባና የተስማማ የመሰለው ተግባብቶና ተስማምቶ ብቻ አይደም፡፡ ጊዜው የጆሮ ጊዜ ስለሆነነው እንጂ፡፡

የቀንዱ ዘመን ሲመጣ ጠያቂ፣ መርማሪ፣ ተከራካሪ፣ ሞጋች ተች፣ ይበዛል፡፡ በፊት የጣመው አሁንይመረዋል፤ በፊት ያስደሰተው አሁን ያስከፋዋል፤ በፊት ዝም ያለው አሁን ያስጮኸዋል፣ በፊት የታገሠውንአሁን ይሰለቸዋል፡፡ በፊት የፈራውን አሁን ይደፍረዋል፡፡ በፊት የተወውን አሁን ያነሣዋል፡፡ ‹ቀኝ ኋላ ዙር›ስለተባለ ብቻ አይዞርም፡፡፡ አባል ስለሆነ ብቻ የድርጅቱን ነገር ሁሉ አይቀበልም፡፡ መለኮታውያን ናቸውያላቸውን መሪዎቹን ሰው አድርጎ መመልከት ይጀምራል፡፡ ላመነው ነገር እንኳ ቢሆን ተጨማሪ ማስረጃይፈልጋል፡፡ የጥንቱን ትርክት ብትተርክ፣ የጥንቱን ዘፈን ብትዘፍን፣ የጥንቱን ፉከራ ብትፎክር እንደ ሞኝ ይቆጥርሃል፡:፡ ያ ሁሉ የጆሮ ዘመን ታሪክ ነውና፡፡ በዚህ ጊዜ ለምን እንደ ጥንቱ ጆሮውን ስንጎትተውአልተጎተልንም፣ ስንመታው ለምን አልሄደም፣ ስንስበው ለምን አልተሳበም፤ ስንቆነጥጠው ለምንአልተቆነጠጠም ብለው የሚያስቡ ዘመንን ማንበብ የማይችሉ ናቸው፡፡ አሁን የቀንድ ዘመን ነው፡፡ የጆሮጊዜ አልፏል፤ ማሳመን ማግባባት፣ ማስረዳት፣ ይፈልጋል፡፡ መስማት ብቻ ሳይሆን መሰማትም ይሻል፡፡

እርጅና በየዘመኑ ነው፡፡ ልጅነት በዘመኑ ያረጃል፤  ወጣትነትም በጊዜው ይጠወልጋል፤ ድርጅትና ማኅበር፤ ተቋምና ፓርቲ በዘመናቸው ያረጃሉ፡፡ ብልህ እንደ ንሥር ያድሳቸዋል፡፡ እንደ እባብ ቆዳ ለዘመኑ የሚመጥን ልብስ ያለብሳቸዋል፡፡ በጆሮ ዘመን የሠሩበትን በቀንድ ዘመን እንሠራበት አይሉም፡፡ እባብ ያድግና ቆዳው አላላውስ ሲለው ቆዳውን ገሽልጦ ጥሎ ለዕድገቱ የሚስማማ ቆዳ ይለብሳል፡፡ ድርጅትና ፓርቲም እንዲህ ካልሆኑ እርጅናው ሞትን ያመጣል፡፡ የጆሮ ዘመን ሲያረጅ ለቀንዱ ዘመን ተዘጋጅ፡፡

ቤተ እምነቶች በዘመናችን ያልተረዱት ቁም ነገር ይሄ ነው፡፡ አንተ ምእመን ነህ ዝም ብለህ ገንዘብህን ስጥ፣ የምንልህን ብቻ ተቀበል፣ ለምን? የት? መቼ? እንዴት? ብለህ አትጠይቅ፤ አባቶችህ ከአንተ በላይ ያውቃሉ፤ አገልጋዮቹ ከአንተ ይሻላሉ፤ አትከራከር፣ ቁጣ፣ መቅሰፍት፣ መዓት ይወርድብሃል፣ ስለተባለ ብቻ የሚቀበልበት የጆሮ ዘመን አልፏል፡፡ መስጠት ብቻ ሳይሆን የሰጠው ገንዘብ የት እንደዋለ ማወቅም ይፈልጋል፤ አባቶቹን ማክበር ብቻ ሳይሆን ክብራቸውን ሲጠብቁ ማየትም ይፈልጋል፤ የሚባለውን መስማት ብቻ ሳይሆን ለሚባለው ነገር ማስረጃም ይሻል፤ ይመዝናል፤ ያመዛዝናል፤ የጥንቱን ከዛሬው፣ ድርጊቱን ከሕጉ ያመሳክራል፤ በሕጋዊው ቤት ሕገ ወጥነት፣ በመንፈሳዊው ቤት ዓለማዊነት፣ በእግዚአብሔር ቤት ቄሣር፣ በጽድቁ ቤት ርኩሰት ሲሠለጥን እያየ ዝም የሚልበት የጆሮ ዘመን አልፏል፤ አሁን የቀንድ ጊዜ ነው፡፡

ተገለጠልኝ፣ ታየኝ፣ በራልኝ፣ ወረደልኝ፣ ፈለቀልኝ፣ ሰማይ ደርሼ መጣሁ፤ አሥር ሺ ሰይጣን አወጣሁ ስላልክ ብቻ የሚቀበልበት የጆሮ ዘመን አልፏል፡፡ ይመዝነዋል፣ ይፈትነዋል፤ ያነጥረዋል፣ ያበጥረዋል፡፡ ‹ኩሎ አመክሩ ወዘሠናየ ግበሩ› ነውና የተባለው፡፡ ከቻለ ይሞግትሃል፤ ካልቻለ ትቶህ ይሄዳል፡፡ ዝም ብለህ ተቀበል የሚባልበት የጆሮ ዘመን አሁን የለም፡፡ እንደ ጆሮው ዘመን ወደፈለግከው አዳራሽና ጸሎት ቤት፣ ወደፈለግከው የራእይና የተአምራት ቦታ አትጎትተውም፡፡ አሁን አልሄድም ብሎ ሊወጋህም ይችላል፡፡ በዚህ ዘመን በየቤተ እምነቱ በምእመናኑና በእምነት አለቆች መካከል የምናየው ውጊያ ይሄ ነው፡፡ ወደፈለግነው አቅጣጫ እንጎትታለን በሚሉ የጆሮ ዘመን አለቆችና ‹ቀንዴ ከፍ ከፍ አለ› በሚሉ ቀንድ ባበቀሉ ምእመናን መካከል፡፡

ድርጅትህን ስትመሠርተው ልጅ ስለነበር እንደፈለግክ ታደርገው ይሆናል፡፡ እየሰፋ፣ እያደገ፣ እየተለጠጠ፣ እየታወቀና እየሠለጠነ ሲሄድ ግን ከጆሮው ዘመን አልፎ የቀንዱ ዘመን ላይ ይደርሳል፡፡አንተ ድርጅቱን መምራት ብቻ ሳይሆን ድርጅቱም አንተን ሊወጋህም ይችላል፡፡ ብዙዎች በገዛ ድርጅታቸው ቀንድ ተወግተው ታሥረዋል፣ ከሥረዋል፣ ጠፍተዋል፣ በሽተኞች ሆነዋል፡፡ ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል፤ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ ብልህ ነጋዴ በጆሮው ዘመን ቀድሞ ያስባል፡፡ እንደ ጥንቱ እመራዋለሁ፣ አስተዳድረዋለሁ፣ እኔ እበቃዋለሁ፣ ለዚህ ደግሞ መቼ አንሳለሁ አይልም፡፡ የልጅነቱን ልብስ አሁን ልልበስ እንደማይለው ሁሉ የጥንቱን አሠራር አሁን ልከተል አይልም፡፡ ለቀንዱ ዘመን የሚመጥን አሠራር፣ ሥርዓት፣ አስተዳደር፣ ባለሞያ፣ ሕግ፣ አደረጃጀት፣ የደረጃ ምጣኔና አስተሳሰብን ይገነባል እንጂ፡፡

በሀገራችን ዘመን ተሻግሮ ከልጅ ልጅ የሚተርፍ ድርጅት ያጣነው፣ ባለቤቶቹ ድርጅቱን በጆሮው ዘመን አስተሳሰብ በቀንዱ ዘመን እንምራው ስለሚሉ ነው፡፡፡ ድርጅቱ አድጎ አድጎ ከዐቅማቸው በበላይ ይሆንና ያሳደገው አውሬ እንደሚበላው አዳኝ ያሳደጉት ድርጅት እነርሱንም ይበላቸዋል፡፡ ስንት ዘመን መርቼው፣ ድንጋይ ጥዬ መሥርቼው፣ ላቤን ጠብ አድርጌ እዚህ አድርሼው ማለቱ አይጠቅምም፡፡ ያ የጆሮ ዘመን ነውና፡፡

ምንጭ:- የዳንኤል ክብረት እይታዎች

Advertisement