የሴት ልጅ ግርዛት – ዘመን ያልፈታው ቋጠሮ – በመስከረም አያሌው

 

በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ብቻ በሁለት መቶ ሚሊዮን ሴቶች ላይ ግርዛት ተፈፅሞባቸዋል። ይህ አሃዝ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከነበረው ግምት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በ70 ሚሊዮን ብልጫ አሳይቷል። ከሁሉ ነገር የበለጠ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደረገው ደግሞ ሁለት መቶ ሚሊዮን ግርዛት የተፈፀመባቸው ሴቶች የሚገኙት በሰላሳ ሀገራት መሆኑ ነው። በተባበሩት መንግስታት በየዓመቱ በፈረንጆቹ ፌብሩዋሪ 6 የሚከበረውን ዓለም አቀፉን የሴት ልጅ ግርዛት ቀን አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የህፃናት መረጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ይህን አስደንጋጭ ቁጥር እና እውነታ ይፋ አድርጎታል።

የሴት ልጅ ግርዛት በአብዛኛው በታዳጊ ሀገራት ባሉ ሴቶች ላይ እየተፈፀመ ያለ ቢሆንም አሳሳቢነቱ ግን የመላው ዓለም እየሆነ መምጣቱን ነው ድርጅቱ የገለፀው። በዚሁ የሴት ልጅ ግርዛት እጅግ አስከፊ የሆነ በደል የደረሰባቸው ደግሞ በተለየ መልኩ በሶስት ሀገራት ያሉ ሴቶች ናቸው። እነዚህ ሀገራትም ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ ናቸው። በሰላሳ ሀገራት ውስጥ ከተፈፀሙ ሁለት መቶ ሚሊዮን ግርዛቶች መካከልም ግማሽ ያህሎቹ የተፈፀሙት በእነዚህ ሶስት ሀገራት መሆኑን ነው ድርጅቱ በሪፖርቱ ያስቀመጠው።

ግርዛት ከተፈፀመባቸው ሁለት መቶ ሚሊዮን ሴቶች መካከል 44 ሚሊዮኖቹ ለዚህ አሰቃቂ ድርጊት የተጋለጡት እድሜያቸው 14 ዓመት እና ከዚያ በታች ሳለ ነበር። በዚህም መሠረት በተደረገው ጥናት በጋምቢያ ከተፈፀመው ግርዛት 56 በመቶዎቹ እና ሞሪታኒያ 54 በመቶዎች እድሜያቸው ገና 14 ዓመት ያልሞላቸው መሆናቸው ተገልጿል። ጉዳዩ አሳሳቢ ነው በተባለበት ኢንዶኔዥያ ደግሞ ግማሽ ያህሎቹ ሴቶች የተገረዙት እድሜያቸው 11 ዓመትና ከዚያ በታች እያለ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ግን በሶማሊያ 98 በመቶዎቹ፤ በጊኒ 97 በመቶዎቹ እንዲሁም በጅቡቲ 93 በመቶዎቹ ከ15 እስከ 49 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የተገረዙ ናቸው። ከዚህ ውጪ ግን በአብዛኞቹ ሀገራት ግርዛት የሚፈፀምባቸው ሴት ልጆች ገና ተወልደው አምስት ዓመት ሳይሞላቸው እንደሆነ ነው ሪፖርቱ ይፋ ያደረገው።

የሴት ልጅ ግርዛት በግልፅ ያልታየ ነገር ግን በአደጉ ሀገራት ጭምር እየተተገበረ ያለ ዘመናዊ የሴት ልጅን መብት መንጠቂያ ድርጊት ሆኗል። ድርጅቱ የሴት ልጅ ግርዛት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ሲል ነው ያስቀመጠው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ በአብዛኛው ድርጊቱ የሚፈፀመው ከሴቶቹ ፍቃድ ውጪ በመሆኑ ነው። ዩኒሴፍ ቅኝት ባደረገበት ወቅት ለአብነት ያህል በጊኒ የሚገኙ ሴቶች እንዲገረዙ እና ድርጊቱን አሜን ብለው እንዲቀበሉ ከቤተሰብ ያለፈ ጫና እንዳለባቸው ነው የገለፀው። እድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ዓመት ከሆኑ የጊኒ ሴቶች መካከል 97 በመቶዎቹ ተገርዘዋል ያለው ድርጅቱ፤ በዚህች ሀገር የሚገኙ ሴቶች እንዲገረዙ የአካባቢ ባለስልጣናት የማስገደድ ስልጣን በማህበረሰቡ እንደተሰጣቸው እና ሴቶቹ ያለፈቃዳቸው ወደ ጫካ ተወስደው እንዲገረዙ እንደሚደረግ ነው ያስረዳው።

የሕዝብ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ የሚገረዙ ሴቶች ቁጥርም የዚያኑ ያህል እያሻቀበ መጥቷል ይላል ዩኒሴፍ። ይህ ድርጊት ታዲያ በአደጉት ሀገራትም አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። የእንግሊዝ ጤና እና ማህበራዊ አገልግሎት ማዕከል በ2015 ባደረገው ጥናት አረጋግጫለሁ እንዳለውም በሀገረ እንግሊዝ በአንድ ዓመት ብቻ 4ሺህ 989 ሴቶች መገረዛቸው ሪፖርት ተደርጓል። በሶስት ወራት ውስጥም ከአንድ ሺህ በላይ ሴቶች መገረዛቸውን ሪፖርት ሲያደርጉ፤ አንድ ሺህ የሆኑት ደግሞ በደረሰባቸው የመገረዝ አደጋ ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል። ከእነዚህ ሴቶች መካከል ደግሞ ዘጠኙ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ሆኖ ተገኝቷል። የሴት ልጅ ግርዛት በእንግሊዝ ከህገ- ወጥ ድርጊቶች ተርታ የተፈረጀው እና በሕግ የተከለከለው እ.ኤ.አ. ከ1985 ጀምሮ ነበር። ይህ ሕግ ሴት ህጻናት ከእንግሊዝ ወደሌላ ቦታ ሄደውም ቢሆን ግርዛት እንዳይፈፀምባቸው የሚከለክል ህግን ጨምሮ ቀድሞ የወጣው ሕግ በ2003 እ.ኤ.አ. እንዲሻሻል ቢደረግም፤ ድርጊቱ ግን አሁንም ድረስ እየተተገበረ ይገኛል።

የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት ይፋ እንዳደረገውም የሴት ልጅ ግርዛት በአብዛኛው በምዕራብ፣ ምስራቅና ሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት እንዲሁም በእስያ እና መካከለኛው ምስራቅ ባሉ ሀገራት ነው የሚተገበረው። በይበልጥ ተጠቂ ናቸው በተባሉ አፍሪካዊያን ሴቶች ዘንድ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ በየዓመቱ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ሴቶች የዚህ ድርጊት ሰለባዎች መሆናቸውን ድርጅቱ ገልጾ ነበር። ምንም እንኳን ድርጊቱ በመላው ዓለም ላይ አሳሳቢ እየሆነ ቢመጣም በተለይ በአፍሪካ ያለው ተፅዕኖ ግን ተደራራቢ ነው ተብሏል።

በኢትዮጵያ የሴት ልጅ ግርዛት ረጅም ታሪክ ያለውና አሁንም ድረስ በስፋት እየተተገበረ ያለ ድርጊት ነው። እንደየአካባቢው ይህ ድርጊት የሚፈፀምባቸው የተለያዩ ምክንያት እንዳሉም ነው የሚገለፀው። እ.ኤ.አ. በ2014 ባዩ ሜድ ሴንትራል በተባለ ተቋም በተደረገ አንድ ጥናት ላይ ከተሳተፉት 634 ሴቶች መካከል 486ቱ ግርዛት የተፈፀመባቸው ሆነው ተገኝተዋል። እነዚህ ሴቶችና የአካባቢ ሽማግሌዎች እንደገለፁትም አንዲት ሴት መገረዝ ያለባት የሚያገባት ባል ላለማጣት፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ጥሩ ተቀባይነት እንድታገኝ፣ ድንግልናዋን ጠብቃ እንድትቆይ፣ ከፍተኛ የሆነ እና ከማህበረሰቡ ወጣ ያለ (ከወንዱ ፍላጎት) የበለጠ የወሲብ ፍላጎት እንዳይኖራት ለማድረግ እንዲሁም በእምነት ምክንያት በማሰብ እንደሆነ ነው።

ግርዛት የተፈፀመባቸው ሴቶች እንደገለፁትም ከተገረዙ በኋላ ከመጠን በላይ ለሆኑ ውስብስብ ችግሮች ተጋልጠው ነበር። ከዋናነት ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ፣ ቁስለት፣ ሽንትን መቆጣጠር አለመቻል እንዲሁም በብልታቸው አካባቢ እብጠት መፈጠር አጋጥሟቸው እንደነበረ ከልምዳቸው ተነስተው ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የሴት ልጅ ግርዛት የሴቶች ሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመሆንም በዘለለ በህይወት ዘመን ሁሉ የሚከተልን ጥላ የሚያጠላ ችግር እንደሚያስከትል አስቀምጧል። ድርጊቱ ከሚፈጥረው ጠንካራ የህመም ስሜት እና የህዋሳት መጎዳት የተነሳ ለመካንነት፣ ለፌስቱላ በሽታ፣ በወር አበባ ወቅት ለሚፈጠር ችግር፣ መድማት፣ ማመርቀዝ እንዲሁም የአንዳንድ ህዋሳት ስሜት አልባና የደነዘዙ መሆን ያስከትላል ይላል ድርጅቱ።  ጉዳዩ በዚህ ሳያበቃ በሴቷ ቀጣይ ህይወት ላይም የሚያሳርፋቸው ጥቁር ነጥቦች በርካታ ናቸው። ለአብነት ያህልም የተገረዙ ሴቶች ሲያረግዙ የመውለጃ ጊዜያቸው ያልደረሰ ልጆች ለመውለድ የተጋለጡ ይሆናሉ። የሚወልዷቸው ልጆች የቀጨጩ እና ከሚፈለገው ክብደት በታች ያላቸው መሆን፣ እንዲሁም ከተገረዘች እናት የሚወለዱ ህጻናት በሚፈጠሩባቸው የተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ከሌሎች በተለየ ሁኔታ የመሞት እድላቸው ከፍተኛ ነው ተብሏል።

በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ግርዛት እንደየ አካባቢው የተለያየ ቢሆንም ዞሮ ዞሮ ጉዳቱ ከፍተኛ እንደሆነ ነው የተጠቆመው። ለድርጊቱ የተጋለጡ ሴቶች ቁጥር ከተገመተው በላይ እየጨመረ በመምጣቱ ሀገራት የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የየራሳቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም ሀገራት ባደረጓቸው እንቅስቃሴዎች በተለይ እድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ባሉ ሴቶች ላይ የሚፈፀመውን ግርዛት በተወሰነ ደረጃ መቀነስ ተችሏል። ምንም እንኳን መቀነስ የታየው ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ቢሆንም በላይቤሪያ በ41 በመቶ፣ በቡርኪናፋሶ በ31 በመቶ፣ በኬንያ ከ30 በመቶ እንዲሁም በግብፅ በ27 በመቶ መቀነስ ተችሏል ይላል የዩኒሴፍ ጥናት ።

ድርጊቱን በማውገዝ እስከነጭራሹኑ ለማስወገድ በተደረሰ ስምምነትም ከ2008 ጀምሮ 20 ሀገራት ከስምምነት ላይ ደርሰው ነበር። ነገር ግን አሁን እየታየ ያለው ነገር እየተኬደበት ያለው ፍጥነት ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር ብዙም ችግሩን እየፈታው እንዳልሆነ ነው ያለው ዩኒሴፍ የገለፀው። አያይዞም ችግሩ አሁን ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ እና አፋጣኝ መፍትሄ ካልተወሰደበት በቀጣዮቹ 15 ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚሄድ ስጋቱን ገልጿል። የፀረ ሴት ልጅ ግርዛት ቀን በየዓመቱ እየተከበረ ያለውም በ2030 ሀገራት የሴት ልጅ ግርዛትን ለማጥፋት የቤት ስራዎቻቸውን እንዲሰሩ በማስታወስ ነው።

ምንጭ: ምሕደረ ጤና ዶት ኮም

Advertisement